የአዲስ አበባ የገነባችው ፍቱን መዳኛ

በመኮንን ተሾመ ቶሌራ

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ (ሸገር) ሁለት ጊዜ ነው የተወለደችው፡፡ መጀመሪያ መፈናፈኛ የሌላት ሆና፤ ቀጥሎ ደግሞ በንጹህ ወንዞች፣ በህዝብ መናፈሻዎችና ፓርኮች፣ ብስክሌት መንገዶች እና በወንዝ ዳር የእግረኞች መንገድ ያላት ሸገርን ሆና!

የ4.6 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ የሆነችው ይህች ከተማ እንደገና የተወለደችው አዲስ አበባን የማሳመር አላማ ባለው “ሸገርን ማስዋብ” በተሰኘው የመልቲ ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት አማካኝነት ነው፡፡ ይህ የ29 ቢሊዮን ብር (1.028 ቢሊዮን ዶላር) የወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት ቀስ በቀስ ከተማዋን አረንጓዴ የሚያደርግ ነው፡፡ በፈረንጆቹ ፌብሩዋሪ ወር 2019 የተጀመረው በከተማዋ የሚገኙትን ሁለት ወንዞች የማልማትና መልሶ የማገገም ስራዎች ለውጥ በማሳየት ላይ ናቸው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሺነት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት፤ በሶስት አመታት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን፤ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጰያኖችና ለተወሰኑ ቻይናዎችም ጭምር የስራ እድልን ፈጥሯል፡፡

ፕሮጀክቱ የሚተገበረው ከእንጦጦ ተራራቾች ተነስተው በከተማዋ በኩል አልፈው አቃቂ ወንዝ ድረስ በሚጓዙና በአጠቃላይ 51 ኪሎ ሜትሮች በሚሸፍኑ በከተማዋ ሁለት ትልቅቅ ወንዞች ላይ ነው፡፡

የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር አለም አሰፋ “እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ መፍትሔነት የወንዝ ዳር ፕሮጀክቱ፤ ጎርፍና የማዕበል ውሀን መቋቋም የሚችሉ የውሀ መውረጃ ቦዮችን ይተክላል፡፡ የውሀ ማከማቻንና ጥቅምን ያሻሽላል” ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ አየር ንብረት መለወጥ

በአዲስ አበባ የሙቀት መጠን መጨመር፣ ድርቅ እና ደራሽ ጎርፍን ጨምሮ ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮ ሐብቶችና በከተማዋ ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን አሳድረዋል፡፡

ኦፕን አክሰስ በተባለ ተቋም የተካሔደ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ላይ ያተኮረ ጥና ከተማዋ ለአየር ንብረት ተጽዕኖዎች ተጋላጭ መሆኗን አረጋግጧል፡፡

“የተጋላጭነት መጠን የተለያዩ መንስኤዎች በዋናነትም በአየር ንብረት መመዘኛ የክፍለ ከተሞች የዝግጁነት አቅሞች፣ ቀበሌ ተኮር ባህሪዎች እና ለውጦች ባላቸው ትስስር አባሪነት የሚቀርብ ነው” በማለትም በአጽንኦት ይገልጻል፡፡

የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር አለም አሰፋ በአዲስ አበባ ለኢንፎ ናይል እንደገለጹት፤ የግሪን ሀውስ ጋዞች ልቀትን በግልጽ ለመቀነስ አስፈላጊ እርምጃዎች ካልተወሰዱ ከተማዋ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እንደሚገጥሟት ሳይንሳዊ ማሳያዎች ማስገንዘባቸውን ነው፡፡

ኮሚሽነሩ ጨምረው እንደሚገልጹትም “በቀጣይ አመታት የከተማዋ ማስተር ፕላን ከተጎዳ፤ በተለይም ደግሞ የከተማ አረንጓዴ አካል ከተጎዳ እና ከትራንስፖርት እና ከኢንደስትሪዎች የሚወጡትን ጨምሮ የግሪንሀውስ ልቀቶችን በቀጣይ አመታት መቆጣጠር ካልተቻለ የመከማቸት ሁኔታቸውን እየጨመረ በመሄድ ለከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ጉዳቶች ይዳርጋሉ”

እንደ ኮሚሽነር አለም ገለጻ ከሆነ በአዲስ አበባና አጎራባች አካባቢዎች በአየር ንብረት ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ምክንያቶች መካከል የጋዝ ልቀቶች፣ የከተማነት መስፋፋት እና የግብርና እንቅስቃሴዎችን የመሳሰሉ የመሬት አጠቃቀም ለውጦች ናቸው፡፡

አዲስ አበባን ለአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ ማድረግ

የወንዞችና ወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የወንዝ ዳር አካባቢዎች በማቀድ፣ በመንደፍ እና በማስተዳደር የወንዞችን ብክለትና መድረቅ አካባቢያዊ ተጽዕኖዎችን መቀልበስን ያለመ ነው፡፡

በከተማ ኢንደስትሪ አካባቢ የአየር ብክለትን ለመቆጣጠርና ለመቀነስ አረንጓዴያማ ማድረግ የሚመከር መሆኑን ኮሚሽነር አለም ይናገራሉ፡፡

“ካርበን በእጽዋት እድገት ሒደት ተገፍቶ የሚመጣ ነው፡፡ ይኸውም ካርበን በእጽዋት ህዋስ ስሪት የሚያዝ ሲሆን፤ ተክሎች ለእድገታቸው በጸሀይ ብርሀን አማካኝነት ከካርቦንዳይ ኦክሳይድ እና ከውሀ ንጥረ ነገሮችን በሚሰሩበት ሂደት (photosynthesis) ደግሞ ኦክሲጅን ይለቀቃል፡፡ ቅርንጫፎች፣ ቅጠሎች እና ሌሎች ወደ ደኑ መሬት የሚገቡ ነገሮችም እስከሚፈራርሱ ድረስ ካርበንን ያከማቻሉ” በማለት አለም አሰፋ ያስረዳሉ፡፡

አቶ አለም አክለውም በመጓጓዣዎች፣ በኢንደስትሪ ዘርፎች እና ግንባታዎች ካሉት ውጤታማ ቴክኖሎጂዎች ባሻገር፤ አረንጓዴ ልማትን ጨምሮ አረንጓዴ መሰረተ ልማቶች አዲስ አበባ የአየር ንብረት ለውጥን እንድትቋቋም ያግዛሉ ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተበከሉ ወንዞች

ከአካዳሚና ከምርምር ተቋሞች የተገኙ በርካታ የጥናት ውጤቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ከመኖሪያ ቤቶች በሚወጡ ውጋጆች እና በውሀ አካላት አካባቢ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች መገኘት የተነሳ የአዲስ አበባ ወንዞች በከፍተኛ ሁኔታ ተበክለዋል፡፡

ለአብነት ያህልም የአቃቂ ወንዝ የውሀ ኬሚካል ይዘት ላይ የተጠናውና በ2017 በሪሰርች ጌት ለህትመት የበቃው የዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው የውሀው ጥራት ከሰው ልጆች ጋር ተያያዥነት ያለው ባህሪ አሳይቷል፡፡ ለዚህም ከኢንደስትሪ ውጋጆች፣ ከመኖሪያ ቤት ቁሻሻዎች እና የግብርና ስራዎች ጋር የተያያዙ የሰው ልጆች ተጠቃሾ ናቸው፡፡

ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ በመሆኑም መንግስት ከሀገር ውስጥና አለምአቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የውሀ ብክለት ላይ ተጨማሪ ትንተናዎች እንዲሰሩ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ የቆዳ አምራች ፋብሪካዎችና የኬሚካል ኢንዱስትሪዎችን አይነት በካይ ኢንደስትሪዎች ላይም አስፈላጊውን እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

የህንድ የሳይንስ እና አካባቢ ማዕከል ዳይሬክተር ሱኒታ ናሬን፤ ኒውዴልሂ ላይ በቅርቡ ለዚህ ዘጋቢ እንደገለጹት በወንዙ ዙሪያ ክብደት ያላቸው ብረቶች ክምችትን ለመለየት እና መፍትሔዎችን ለማቅረብ ማዕከላቸው የአቃቂ ወንዝን የኬሚካል ትንተና ይፋን አድርጓል፡፡ የመኖሪያ ቤት ቁሻሻዎች፣ ወደ ወንዙ የሚገቡ ፍሳሾች እና የሚጣሉ ፕላስቲክ መገልገያዎች በአዲስ አበባ ወንዞችን ከሚበክሉ መንስኤዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ጎርፍን መቆጣጠርና መመከት

ከጎርፍ ጋር ተያያዥነት ያለውና በሳይንስ ዳይሬክት 2016 የተካሔደው “በአየር ንብረት ለውጥና የከተማነት መስፋፋት የተነሳ የአዲስ አበባ ከተማ የጎርፍ ስጋት እና ተጋላጭነት” የተሰኘ ጥናት እንደሚገልጸው፤ የአቃቂ ውሀ ማከማቻ አካባቢ የከተማነት መስፋፋት መጠን ከ1993 እስከ 2002 10 በመቶ ብቻ ነው ያደገው፡፡ በአዲስ አበባ የጎርፍ ስጋቶችም እንዲሁ በጉልህ መጨመራቸው ተመልክቷል፡፡

ጥናቱ በከፍተኛ የአየር ንብረት ክስተቶች እና በላይኛው የውሀ ማከማቻ ቦታ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት ለሚከሰት ደራሽ ጎርፍ የአዲስ አበባን ተጋላጭነት መለየት የቻለ ሲሆን፤ ደካማ የፍሳሽ ማስወገጃ መንገድ፣ በወንዝ ዳርቻዎች በኩል በፍጥነት የተካሔዱ የቤት ግንባታዎች እና ያልተገቡ የግንባታ መሳሪያዎችን መጠቀም የጎርፍ ተጋላጭነቷን አባብሰውታል፡፡

ስለዚህም የወንዝዳር ልማት ፕሮጀክቱ የወንዝ ጎርፍን በመከላከል፣ የህዝብ መናፈሻዎችን እና ፓርኮችን፣ የብስክት መንገዶችን እና የእግር መንገዶችን በማዘጋጀት የነዋሪዎችን ደህንነት ለማሳደግ እና የከተማዋን ገጽታም ከፍ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

“የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ወደ ወንዞች የሚገቡትን ደለሎች እና ሌሎች በካዮችን መጠን ይቀንሳል፤ ለኑሮ ምቹ የሆኑ አረንጓዴ የከተማ ማዕከሎችን ይፈጥራል፡፡ ይህንንም ከተለያዩ ወንዝ አልሚ ቀጠናዎች ተስማሚ ዛፎችን፣ ቁጥቋጦዎችን፣ ቅጠሎችንና ሳሮችን በመትከል ወንዙ

በተሽከርካሪ እንቅስቃሴዎች እና በተለያዩ የኢንደስትሪ ስራዎች ለሚመነጩ ቅንጣትና ጋዝነት ላላቸው ልቀቶች ልክ እንደ ብቁ ተፈጥሯዊ ማጣሪያዎች የሚያገለግሉ የተለያዩ ወንዝ አልሚ ቀጠናዎችን ከማዘጋጀት ጎን ለጎን በተስማሚ ዛፎች፣ ቅጠላቅጠሎች፣ ተክሎች እና ሳሮች ተከላ አማካኝነት ይከናወናሉ” ሲሉ ኮሚሽነር አለም ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባን ወደ አረንጓዴያማ፣ ምቹና ደስተኛ ከተማነት መለወጥ

እጅጉን ልዩ ከሆነው የወንዝዳርን አረንጓዴ የማድረግ እና አዲስ አበባን የማስዋብ ጥረት ባሻገር የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንአቀፍ ተስማሚ የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታዎችን እና የመከላከያ አቅጣጫዎችና ፖሊሲዎችን በመቅረጽ በጥብቅ እየተገበራቸውም ነው፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለማተኮር በየአመቱ ወደ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠይቀው እቅድ በውስጡ በአዲስ አበባ የአትክልት መናፈሻዎችንና የእንስሳት መናፈሻ ማዕከሎች፣ የወንዝ እና ወንዝ ዳርቻዎች ልማት፣ የእንጦጦ እና ዙሪያው የቱሪስት መዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የተቀናጁ ፕሮጀክቶች ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ፓርኮች ልማት ፕሮጀክቶችን ደግሞ በጁላይ ወር 2018 በተቋቋመው የወንዝ ተፋሰሶችና አረንጓዴ አካባቢዎች ኤጀንሲ ስር እየተከናወነ ነው፡፡

አንድ የምሁራን ስብስብ በአዲስ አበባ የአረንጓዴ ቦታዎች ላይ ወቅታዊ ሁኔታ እና አያያዝ  ልምድ ላይ በማተኮር ያዘጋጀውና የሚል ርዕስ ያለው የቅርብ ጊዜ ጥናታቸው ላይ የአዲስ አበባ የተቀናጀ የአረንጓዴ ቦታዎች ልማት ሚና የአየር ሁኔታን ለመጠበቅ እጅግ ጠቃሚ መሆኑንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ጽፈዋል፡፡

በሳምሶን አየናቸው የተሰራ ጥናት እንደሚገልጸው የአዲስ አበባ ከተማ 22,000 ሄክታር መሬትን ለአረንጓዴ ልማት ቦታ ለይታ ይዛለች፡፡ በአዲስ አበባ የህዝብ ፓርኮች ቦታ ክፍፍል መሰረትም ከአስር ክፍለ ከተሞች መካከል ጉለሌ 9.8 ሄክታር መሬት ከፍተኛውን የህዝብ ፓርኮች ቦታ ድርሻን ወስዷል፡፡ ንፋስ ስልክ ደግሞ በ6.2 ሄክታር ተከታዩን ደረጃ ሲይዝ፤ የካ ክፍለ ከተማ 5.6 ሄክታር፣ ቂርቆስ 4.6 እና ልደታ ክፍለ ከተማ 4.4 ሄክታር መሬትን ወስደዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን የከተማ አረንጓዴ ቦታዎችን በቀበሌ፣ ወረዳ እና ከተማ ደረጃ ለይቶ መድቧቸዋል፡፡ በቀበሌ ደረጃ ለፌስቲቫሎች፣ ለህጻናት መጫወቻዎችና ሌሎች እንቅስቃሴዎች የተተው በርካታ ክፍት እና አረንጓዴ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹ በመኖሪያ ቤቶች መካከል ያሉ ክፍት ቦታዎችን የተዋቸው ሲሆን፤ እንደ ከተማ ክፍት ቦታዎች ተደርገው የሚቆጠሩት ደግሞ በጥሩ ሁኔታ አልተያዙም፡፡

በወረዳ ደረጃ ያሉት አረንጓዴ ቦታዎች የመንገድ ዳርቻዎች፣ የገበያ ማዕከሎች፣ እና አብዛኞቹ ክፍት የህዝብ ቦታዎች በከተማዋ መሀል ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ቦታ የገበያ ማዕከሎች፣ አደባባዮች፣ መንገዶች እና ፓርኮች በይፋ የተሰየሙ ናቸው፡፡ የእነዚህን ቦታዎች አያያዝ በአንጻራዊነት ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን አጠቃቀምን በተመለከተ ግን በአግባቡ እያገለገሉ አይደሉም፡፡

በከተማ ደረጃ ያሉት አረንጓዴ ቦታዎች በተራራዎች እና ጥብቅ ቦታዎች የሚገኙ የደን ቦታዎችን ጭምር ያካተቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ቦታዎች ዛፎችን እና ደንን ከመጠበቅ አንጻር በጥሩ ሁኔታ ቢያዙም በቀላሉ የማይገኙና እንደ መዝናኛ ቦታዎች አስፈላጊ ነገሮችን ያላሟሉ በመሆናቸው ሰዎች እንደልባቸው እየተገለገሉባቸው አይደለም፡፡

ለከተማ አረንጓዴ ቦታዎች ዋጋ መስጠት

የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት ከሚሸፍነው ከአጠቃላዩ 51ኪሜ ውስጥ 12 ኪሜ የሚሸፍነው የመጀመሪያው ምዕራፍ ፕሮጀክት በኦክቶበር 2019 በመጀመሩና ቀደም ሲል በተጠናቀቁ የተወሰኑ ስራዎች የአዲስ አበባ መልክን ገጽታ ከፍ ማለቱን መረዳት ተችሏል፡፡ ሰዎችም የአረንጓዴያማ ጥረቶችን ፍሬዎች ማጣጣም ጀምረዋል፡፡ ለአብነት ያህልም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት አካል በሆነው በኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፎር አፍሪካ (ኢሲኤ) ዙሪያ እየተጠናቀቁ ላይ ባሉና ክፍት በሆኑ በተወሰኑ የወንዝ ዳር ልማት ክፍሎች በመገኘት ሰዎች መዝናናት ጀምረዋል፡፡ የውሀ አካላት በመከለልና በመለየት ስራ አማካኝነትም የአዲስ አበባ ወንዞችን የመንከባከብና የማጽዳት ስራዎችም ተጀምረዋል፡፡

አዲስ አበባን የማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነውና በቦሌ አፍሪካ መንገድ ከቦሌ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ አንስቶ እስከ ብሔራዊ ቤተ መንግስት ድረስ የሚካሔደው ለአበባ እንስራዎችና አበባ መትከያዎች የሚሆኑ የብረት ማቀፊያዎች ተከላ ስራ እየተጠናቀቀ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ለጎብኝዎች መልካም ስሜት የሚፈጥር አይን ማረፊያ ሆነዋል፡፡

የከተማ አረንጓዴ አካባቢዎች ለካርበን ስርገት ከፍተኛ ጠቃሚ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የከተማ ዛፎች ለዚህ አላማ ያላቸውን አስተዋጽኦ በመረዳትም የከተማ ዛፎችን የመንከባከብና የመጠበቅ ፍላጎት ጨምሯል፡፡

በእርግጥ ዛፎችን መትከል ለኢትዮጵያ አዲስ ልምድ አይደለም፡፡ በጁላይ ወር 2019 ሰፊ የችግኝ ተከላ ዘመቻ በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተነሳሺነት የተጀመረ ሲሆን፤ አላማውም የሀገሪቷን የተራቆተ መሬት ለመጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለመቋቋም ነው፡፡ ይህም አዲስ አበባን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያን የሸፈነ ነው፡፡ በ12 ሰአታት ውስጥም የአለም ክብረወሰን የሆነ 353,633,660 የዛፍ ችግኞችን በመላው ሀገሪቱ መትከል ተችሏል፡፡

የህዝቡ ስሜት ስለ ፕሮጀክቱ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አሁን ከተማቸው ከምንግዜውም የበለጠ በተሻለና እና በበለጠ ሁኔታ አረንጓዴ እንደምትሆን ተስፋ አድርገዋል፡፡

ተስፋዬ አባተ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ያለውን የአረንጓዴ አብዮት ከሚመሰክሩ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ተግባር ማህበረሰቡን የጎዳውን ድርቅና ጎርፍ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ይናገራል፡፡

“ካለፉት አመታት የበለጠ አረንጓዴ የሆነች ከተማችንን ለማየት ደስተኛ ነኝ፡፡ ይህም እየተባባሰ የመጣውን የአለም ሙቀት መጨመርና አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች ለመቋቋም እንደሚያስችለን ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ አካባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ እንደሚገልጹት የአረንጓዴ ስራ ጥረቶች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› ተብሎ በሚታወቀው ብሔራዊ የአረንጓዴ ዘመቻ አማካኝነት በኢትዮጵያ እየተካሔደ ያለው የወንዝ ዳር ልማትና ከፍተኛ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመታገል ጠቃሚ መሆናቸውን ፕሮፈሰሩ ይስማማሉ፡፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ የሆነ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያላትን ርዕይ የሚያስረዳ አርአያነት ያለው አረንጓዴ እንቅስቃሴ መሆኑንም ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ ገልጸዋል፡፡

ይህ ዘገባ የተዘጋጀው ከኢንፎናይል እና ናሽናል ጂዮግራፊ ሶሳይቲ በተገኘ ድጋፍ ነው