በኮቪድ 19 እንቅስቃሴዎች ሲገደቡ ሴቶችን ካልታቀዱ እርግዝናዎች የታደገው ሀገር በቀል ተቋም

በፍሬድሪክ ሙጊራ

ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሀገሪቱ የተጣለው የእንቅስቃሴዎች እገዳን ለቀጣይ 21 ቀናት መራዘሙን አስታውቀው ነበር፡፡ በወቅቱ ታዲያ በተረራማዋ የዩጋንዳ አውራጃ ቡህዌጁ በምትገኘው ካሴሬሬ ቢሰያ የምትኖረው የቤት እመቤት ቢሩንጊ ጆይስ የጥርጣሬ ስሜት ተሰምቷት ነበር፡፡

ቢሩንጊ በየወሩ የምትቀበለው በአፍ የሚዋጥ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች አልቀውባታል፡፡ መጀመሪያ ላይ ያሰበችው ለ14 ቀን የተጣለው የእንቅስቃሴዎች እገዳ ሲያበቃ ከመኖሪያ ቤቷ 30 ኪሜ ርቀት በሞተር ሳይክል ተጉዛ እንደምትገዛ ነበር፡፡ ነገር ግን የእንቅስቃሴዎች እገዳው እሷ እንዳሰበችው በ14 ቀናት ብቻ አላበቃም፡፡ እገዳው ለተጨማሪ 21 ቀን ተራዘመ፡፡

በዚህም የተነሳ ያላት ብቸኛ አማራጭ መታቀብ ነበር፡፡ ባለቤቷ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡

“ባለቤቴ ወሲብ መፈጸም ባለመቻላችን አንዳንድ ጌዚ ዱላ ሁሉ ይሰነዝርብኝ ነበር” ስትል ሁኔታውን ትገልጻለች፡፡ “እኔ ግን መታገሱን መረጥኩ፡፡ ይህ ለእኔ ልጅ ከመጸነስና ስድስተኛ ልጃችንን ከመውለድ የተሻለ ነበር” ትላለች፡፡

የ35 አመቷ ቢሩንጊ እንደምትገልጸው እሷና ባለቤቷ አምስት ልጆቻቸውን ለማሳደግ መቸገራቸውንና ሌላ ልጅ ለመጨመር አቅማቸው አይፈቅድም፡፡

እናም ምን ማድረግ እንዳለባት ለመወሰን ግራ የተጋባችው ቢሩንጊ በመንደሯ ከሚገኙ ሴቶች አንድ መላ ታገኛለች፡፡ ይኸውም በሴቶች የሚመራው መንግስታዊ ላልሆነው EPHWOR የሚባለው ድርጅት እንዲረዷት እንድትደውልላቸው ነው፡፡

የአካባቢዋ ሴቶች የድርጅቱን ስራና የሃላፊዎቹን ተግባር በተመለከተ በአካባቢያቸው ቴሌቭዥን የተላለፈውን ዘገባ ሲመለከቱ የስልክ ቁጥራቸውን ወስደው ነበር፡፡

ቢሩንጊም ወዲያውኑ ከመንደሯ ሴቶች ስልክ ቁጥር ወስዳ ወደ ድርጅቱ የስራ ሀላፊዎች ትደውላለች፡፡ ከአንድ ቀን በኋላም የድርጅቱ ሰዎች ወደ መንደሯ በመምጣት ለሁለት ወራት የሚሆናትን የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን ሰጥተዋታል፡፡

ሰባት ሚሊዮን ያልተፈለጉ እርግዝናዎች

ቢሩንጊ ይህንን እገዛ ባታገኝ ኖሮ ላተፈለገ እርግዝና ልትጋለጥ ትችል ነበር፡፡ እናም የተባበሩት መንግስታት በኮቪድ 19 አማካኝነት የእንቅስቃሴዎች እገዳ ለ6 ወራት ከቀጠለና ዋና ዋና አገልግሎቶች ከተቋረጡ ሊከሰት ይችላል ብሎ ከገመተው 7 ሚሊዮን ያልተፈለጉ እርግዝናዎች መካከል የእሷም አንደኛው ሆኖ ሊመዘገብ ይችል ነበር፡፡ 

አሁን ግን ብሩንጊ EPHWOR ማለትም Enforcement of Patients and Health Workers’ Rights Uganda የተሰኘው ተቋም በዩጋንዳ በኮቪድ 19 የእንቅስቃሴዎች እገዳ ወቅት በስምንት ወረዳዎች ውስጥ ካልተፈለገ እርግዝና ከታደጋቸው 300 ሴቶች መካከል አንዷ ለመሆን ችላለች፡፡

እነዚህ ሴቶች በምባራራ፣ ኢባዳ፣ ቡሃውጁ፣ ሺማ፣ ኢሲንጊሮ፣ ርዋምፓራ፣ ኪሩሁራ እና ካዞ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ 

በሴቶች ጤና እና መብቶች ላይ የሚሰራው ይህ ድርጅት ስራውን የጀመረው በ2017 ነው፡፡ በሴቶች መብቶች መከበርና ድጋፍ፣ የጾታ እና ስነተዋልዶ ጤና እና መብቶች እንዲሁም በገጠርና ከተማ የዩጋንዳ አካባቢዎች የሚገኙ የታማሚዎች መብቶች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ 

ዶክተር አሩሆ አሞን ካቴጋያ በድርጅቱ የሜዲካል እና ስነ-ተዋልዶ ጤና አማካሪ ሲሆኑ፤ ስራቸውን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “ዩጋንዳ የወሊድ መቆጣጠሪያ የመጠቀም ልምድ መጠኗ ጥሩ ለውጥ እያሳየች በመሆኗ ይህ የእኛ እንቅስቃሴም አስፈላጊ ሴቶችን ካልተፈለገ እርግዝና ለመታደግ የሚያስችል ነው” ብለዋል፡

በዩጋንዳ የአንዲት ሴት የመውለድ መጠን በ2020 4.78 መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የህጻናት ቁጥር መመንደግ

በኮቪድ 19 የእንቅስቃሴዎች እገዳ ከተጣለ በኋላ በዩጋንዳና በብዙ ታዳጊ የአፍሪካ ሀገሮች በቤተሰብ ምጣኔ ዘዴዎች ውስጥ የተካተቱ ሴቶችና ልጃገረዶች የወሊድ መቆጣጠሪያዎችን ማግኘት ከባድ ሆኖባቸዋል፡፡ የመጓጓዣ አገልግሎት ላይ እገዳ በመጣሉ ይህ ችግር የተባባሰ ሲሆን፤ ብዙዎችን የወሊድ መቆጣጠሪያ ለማግኘት በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በእግር ተጉዘው ወደ ጤና ተቋማት፣ ክሊኒኮች እና መድሀኒት ቤቶች መሔድ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡

የዩጋንዳ የስነ ተዋልዶ ጤና ተቋም (RHU) የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የሚሰጥባቸው በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ መስኮች ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ መዘጋታቸውም ሁኔታውን ይበልጥ አስከፊ አድርጎታል፡፡

በዩጋንዳ የስነ ተዋልዶ ጤና ተቋም ውስጥ የክሊኒክ አገልግሎቶች ሀላፊ የሆኑት ዶ/ር ኬኔዝ ቡይንዛ በቅርቡ ለኒው ቪዥን ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ሁሉንም አገልግሎት መስጫዎችን ለመዝጋት የተገደዱት “በርካታ ደምበኞቻቸው የሚፈለገውን አራት ሜትር አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ ባህሪን ባለመመልከታቸው ነው”

የምባራራ አካባቢ ሪፈራል ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶ/ር ቴሬስታይን ባሪግዬ እንደተናገሩት ምንም እንኳ የተወሰኑ እናቶች አሁንም ድረስ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ቢሆንም፤ ወደ ጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች የሚያደርሷቸውን የመጓጓዣ መንገዶችን ማጣት በርካታ ሴቶችና ልጃገረዶችን “ተጨማሪ” ልጆችን ለመውለድ ስጋት እንዲጋለጡ ተጽዕኖ ፈጥሮባቸዋል፡፡

“የህጻናት ቁጥር መመንደግ” ልንለው እንችላለን ሲሉም ዶ/ር ባሪግዬ ሁኔታውን ይገልጹታል፡፡ አክለውም “ይህ የሆነበት ምክንያት አሁን ላይ ሰዎች (ጥንዶች) ቤት ውስጥ በመሆናቸው ነው፡፡ ሰዎቹ አንድ ላይ ሲሆኑ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ይቻላል” ብለዋል፡፡ 

ከኮቪድ 19 የእንቅስቃሴዎች እገዳ በኋላ በደቡብ ምዕራባዊ ክልል ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ወራት ድረስ የህጻናት ቁጥር እጅጉን እንደሚጨምርም ዶ/ር ባሪግዬ ተንብየዋል፡፡ 

ባለፈው ወር የዩጋንዳ ቤተክርስትያን ቄስ ስቴፈን ካዚምባ ሙጋሎ፤ ለሴቶች ባስተላለፉት መልዕክት በእንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ በሚጣልበት ጊዜ ሊጸንሱ ስለሚችሉ የወሊድ መቆጣጠሪያዎችን መጠቀማቸውን እንዳይረሱ አስገንዝበው ነበር፡፡

“እነዚያ ወንዶች አጠገባችሁ ናቸው፡፡ ምግብ ይበላሉ፤ አንዳንድ ነገሮችንም ያደርጋሉና ተጠንቀቁ!” በማለት ቄስ ዶ/ር ካዚምባ ካምፓላ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሆነው በብሔራዊ ቴሌቭዥን ባስተላለፉት ስብከት ላይ አሳስበው ነበር፡፡ 

በ241,037ኪሜ ስኩዌር በምትገኘው ሀገር ላይ የዩጋንዳ የህዝብ ብዛት በ2060 ላይ 103.5 ሚሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡

በጥቂት ሀብቶች ላይ የተጫነው ሸክም

በቤተሰብ ውስጥ ተጨማሪ ልጅ ማከል በተለይም ደግሞ ያለ እቅድ የሚፈጠር ልጅ የቤተሰቡ የኑሮ ሀብቶች ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡ ይህም ልክ የህዝብ ብዛት መጨምርና በሀገር ሀብቶች ላይ አሉታዊ ጫናዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት እንደሚሆነው ማለት ነው፡፡  

የገንዘብ እቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የኢኮኖሚ አማካሪ ዊልሰን ትዋሙሃብዋ ካዲዲ የህዝብ ብዛት ቁጥር መጨመር በተለይም ምርታማ ያልሆነ ህዝብ መጨመር “መንግስታት ወይም ቤተሰቦች ባላቸው ውስን ሀብቶች ላይ ተጨማሪ ሸክም ነው” ብለዋል፡፡

“የህዝብ ብዛት መጨመር ባሉት ሀብቶች ላይ ከባድ ሸክምን መጫን ነው፡፡ ምክንያቱም መንግስትና ቤተሰቦች ለነዚያ ለተጨመሩት ሰዎች ማቀድ ይኖርባቸዋልና” ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

ሁኔታው ደግሞ ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ የድህነት ጫናዎችን ለመታገል የቤተሰብ ምጣኔን አማራጭ ላደረጉ በዩጋንዳ ገጠራማ አካባቢ ለሚኖሩት እጅጉን የከፋ ነው፡፡ 

የኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ያለባቸውን ሴቶች መደገፍ

በዩጋንዳ በሴቶች የስነተዋልዶ ጤና መብቶች እና አገልግሎቶች ላይ የተሰማራው EPHWOR የተሰኘው ድርጅቱ ለሴቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶችን ብቻ አይደለም የሚሰጠው፡፡ እንደ ዶ/ር አሩሆ ገለጻ ከሆነ በስምንቱ ወረዳዎች ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶችና ልጃገረዶች የኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ላለባቸው ሴቶች በየወሩ የእድሜ ማራዘሚያ መድሀኒቶችን፣ የካንሰር መድሀኒቶችንና ሌሎች ህክምናዎችን እንዲያገኙም ይሰራል፡፡ 

ድርጅቱ ከመንግስት የጤና ተቋማት ጋር በመተባበር የሚሰራ ሲሆን፤ የምባራራ አካባቢ ሆስፒታል፣ የምባራራ ማዘጋጃ ካውንስል የጤና ማዕከል፣ የሩሁኮ ጤና ማዕከል አራት እና የኒስካ ጤና ማዕከል አራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ክትትል ለሚያደርጉላቸውም ሆነ ለሚያቀርቡላቸው ነጻ መድሀኒቶችንና ክትትል ለማድረግና መድሀኒት ለማድረስ የታማሚዎችን የህክምና ሰነድ ማግኘት ይችላሉ፡፡ 

በህዝብ የጤና ተቋማትና ሐኪም ቤቶች ለማግኘት አዳጋች የሆኑ መድሀኒቶች ደግሞ ድርጅቱ እጅግ ለሚያስፈልጋቸው ሴቶች በሰአቱ እንዲደርሳቸው ገንዘብ ከራሱ ወጪ በማድረግ ይገዛል፡፡ 

ዶ/ር አሩሆ አስረግጠው እንደሚገልጹትም ካንሰርን፣ ኤች አይቪ ኤድስ፣ የሥኳር ህመምን ጨምሮ ከባድ የሚባል ህመም ያለባቸውና በጊዜ ሰሌዳ መድሀኒቶችን የሚወስዱ ሰዎች በኮቪድ 19 የእንቅስቃሴ እገዳዎች ወቅት ፈጽሞ ተዘንግተዋል፡፡

ለሁለት ወራት የእንቅስቃሴ እገዳ በተጣለበት ወቅት ድርጅቱ 40 ሴቶች የኤች አይቪ ኤድስ መድሀኒቶችን በነጻ እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡ ሌሎች 100 ሴቶች ደግሞ የስኳር እና የደም ግፊት መድሀኒታቸውን በነጻ እንዲገኙ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ምግብ ማግኘት ላልቻሉ ለተወሰኑ ሰቶች 1500 ኪሎ ግራም የበቆሎ ዱቄትን አቅርቦላቸዋል፡፡ ለዚህ እንቅስቃሴም በአጠቃላይ ከ10 ሚሊየን ሽልንግ (2700 ዶላር) በላይ ወጪ አድርጓል፡፡ 

በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶችን ለመርዳት ከዚህ ጊዜ የተሻለ መልካም አጋጣሚ የለም ብለዋል ዶ/ር አሩሆ፡፡ 

ይህ በኢንፎናይል በኩል ዘገባ የተጠናከረው ዘገባ ስኬታማ የሆነው በፑልቲዘር ሴንተር ኦን ክራስይስ ሪርቲንግ እና ናሽናል ጆኦግራፊክ ሶሳይቲ ባደረጉት ቀና ድጋፍ አማካኝነት ነው፡፡